መጪው ሀገራዊ ምርጫ እና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ስጋት!
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ተኛ አገራዊ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ አድርጓል። ይህንንም ተከትሎ በሚቀጥሉት ወራት ምርጫን የተመለከቱ መረጃዎች የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ጨምሮ የመገናኛ ብዙሃን የትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
እውነተኛ እና የተጣሩ መረጃዎች መራጮች ስለተፎካካሪ ፓርቲዎች አማራጭ ፖሊሲዎች፣ ስለ ቅድመ ምርጫ፣ ምርጫ እና ድህረ ምርጫ ክንውኖች እና ወዘተ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲይዙ በማድረግ ዜጎች በዕውቀትና በነጻ ፍቃዳቸው ላይ ተመስርተው ወኪሎቻቸውን እንዲመርጡ ይረዳሉ።
በአንጻሩ ሀሰተኛ መረጃዎች ዜጎች በዕውቀት ላይ የተመሰረት ውሳኔ እንዳያሳልፉ ተግዳሮት በመሆን እንዲሁም በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድህረ ምርጫ ሂደቶች እምነት እንዳይኖራቸው በማድረግ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር የጀመሩትን ጉዞ ያውካሉ። ከዚህም አልፎ በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በማህበረሰቦች መካከል አለመተማመን እና ጥርጣሬ እንዲሰፋ በማድረግ ለግጭት በር ይከፍታሉ።
የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት በምርጫው ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የመንግስት አካላት፣ ሚዲያዎች እና መረጃ አጣሪዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ የማህበራዊ ትስስር ገጽ አንቀሳቃሽ ድርጅቶች የራሳቸውን ሚና ለመወጣት ከወዲሁ አቅደው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። ለዚህም የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ተጽዕኖ በመቋቋም የተሳኩ ምርጫዎችን ካደረጉ አገራት በጎ ተሞክሮዎችን መውሰድ ይቻላል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቅድመ ምርጫ፣ የምርጫ እና የድህረ ምርጫ ክንውኖችን በግልጽ፣ በዝርዝር እና በወቅቱ ለዜጎች እንዲደርሱ በማድረግ እንዲሁም ለጋዜጠኞች እና ለመረጃ አጣሪዎች በሩን በመክፈት ሀሰተኛ መርጃ የሚያሰራጩ አካላትን ተጽዕኖ ለመቀነስ ራሱን ማዘጋጅት ይጠበቅበታል። የመንግስት አካላት በተለይም ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመግታት ስለወጡ ህጎች ዜጎች በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐግብሮችን ማዘጋጀት ይኖርበታል።
የሚዲያ ተቋማት በበኩላቸው የጋዜጠኝነት ሙያ መርሆችን በላቀ አግባብ በመተግበር ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ ለማድረስ ከወዲሁ በቂ ዝግጅት ማድረግ እንዲሁም መረጃ የሚያጣሩ ባለሙያዎችን በመመደብ እና በማሰልጠን ሀሰተኛ መረጃ በምርጫው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። በተለይም መረጃን በማጣራት ረገድ በቅርቡ ምርጫ ከተካሄደባቸው አገሮች ሚዲያዎች ጠቃሚ ተሞክሮዎችን መቅሰም ይቻላል።
የሲቪክ ማህበራት፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ዜጎች ስለሚዲያ ንቃት እንዲኖራቸው ለማስተማር ራሳቸውን በማዘጋጀት ሀሰተኛ መረጃ በምርጫው ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ተግዳሮት በመቀነስ በጎ ሚና ለመጫዎት መዘጋጀት አለባቸው።
የማህበርዊ ትስስር ገጾች አንቀሳቃሽ ድርጅቶች ኢትዮጵያውያን የሚናገሯቸውን ቋንቋዎች የሚረዱ በቂ ባለሙያዎችን በመቅጠር የክትትል እና የእርምት ተግባራቸውን በማሳለጥ፣ ሪፖርት ለሚደረጉ ይዘቶች፣ አካውንቶች እና ገጾች ፈጣን ግብረመልስ በመስጠት እንዲሁም የፓርቲዎችን፣ የእጩ ተወዳዳሪዎችን፣ የሚዲያዎችን፣ የጋዜጠኞችን እና የምርጫ አስፈጻሚዎችን አካውንቶችና ገጾች እውቅና በመስጠት (verify በማድረግ) የማህበራዊ ትስስር ገጾች ለሀሰተኛ መረጃ አሰራጮች ምቹ እንዳይሆኑ በማድረግ መጭው ምርጫ በአንጻራዊነት ጤናማ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና መጫዎት ይችላሉ።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::