በቅርቡ በአሜሪካ እክል ያጋጠመው የቦይንግ 777 አውሮፕላን ጉዳይ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ይመለከተው ይሆን?

ባሳለፍነው ቅዳሜ ንብረትነቱ የዩናይትድ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 777 የመንገደኞች አውሮፕላን በቀኝ ሞተሩ ላይ እክል ከገጠመው በሗላ የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር የፕራት እና ዊትኒ 4000 ሞተር የተገጠመላቸው ቦይንግ 777 አውሮፕላኖች ላይ ምርመራ እንዲደረግ መመሪያ አስተላልፏል።

መመሪያውን ተከትሎ ዩናይትድ አየር መንገድ የፕራት እና ዊትኒ ሞተር የተገጠመላቸውን ቦይንግ 777 አውሮፕላኖቹን አሳርፏል። የጃፓን አቪዬሽን ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤትም ተመሳሳይ ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን የኦል ኒፖን እና የጃፓን አየር መንገዶች 34 አውሮፕላኖችን ከስራ ውጭ ለማድረግ ተገደዋል።

ወደ አሜሪካ እና ጃፓን በረራዎችን የሚያደርገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሁለቱ አገሮች አቪዬሽን ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቶች ውሳኔ ይመለከተው እንደሆነ ለማወቅ ኢትዮጵያ ቼክ የአየር መንገዱን የህዝብ ግንኙነት እና ኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ሀላፊ አቶ ሄኖክ ሲራክን ያነጋገረ ሲሆን “የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፕራት እና ዊትኒ ሞተር የተገጠመላቸው ቦይንግ 777 አወሮፕላኖች የሉትም፣ የአቬሽን ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቶች ውሳኔም አይመለከተውም” የሚል ምላሽ አግኝቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ ምርት የሆኑ አራት B777-300ER ፣ ስድስት B777-200LR የመንገደኞች እና አስር B777-200LRF የጭነት አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን ሁሉም የጄነራል ኤሌክትሪክ ሞተሮችን እንደሚጠቀሙ አቶ ሄኖክ ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግረዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::