በቀድሞው ፕሬዚዳንት ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም ጤንነት ዙርያ ማህበራዊ ሚድያ ላይ የሚፃፈው ምን ያህል እውነት ነው?

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም ሀራሬ፣ ዚምባብዌ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ እንዳሉ እና “ነፍስ ውጪ፣ ነፍስ ግቢ” የሚባል ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ኢትዮጵያን ዲጄ የተባለ የፌስቡክ ገፅን ጨምሮ በርካቶች እየፃፉ ይገኛሉ።

እውነታውን ለማጣራት ኢትዮጵያ ቼክ ፋራይ ሙትሳኪ እና አንድሪው ኩናምቡራ የተባሉ ለመረጃ ቅርበት ያላቸው የዚምባብዌ ጋዜጠኞችን አናግሯል። ሁለቱም ከዚምባብዌ ባለስልጣናት እና የህክምና ማእከላት ማረጋገጥ እንደቻሉት መረጃው “ተራ ወሬ” ነው። በፕሬዝደንቱ ዙርያ በርካታ ዜናዎችን ከዚህ በፊት የፃፉት እነዚህ ጋዜጠኞች “ማረጋገጥ የቻልነው በመንግስቱ ዙርያ ምንም አዲስ ነገር እንደሌለ ነው” ብለዋል።

ጦማሪ ወንደሰን ተክሉም ይህንን የሚያረጋግጥ መረጃ ይዞ የወጣ ሲሆን “በኢትዮጵያን ዲጄ የተሰራጨው ዜና ትክክለኛ ያልሆነ፣ የፈጠራ ዜና ነው እንጂ አባቴ በጣም በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ ናቸው” እንዳሉ የኮ/ሉ ሁለተኛ ልጅ የሆኑት ዶ/ር ትእግስት መንግስቱ በስልክ አረጋግጠውልኛል ብሏል።

ዶ/ር ትእግስት ኮ/ል መንግስቱ ከሁለትና ሶስት ዓመት በፊትም በተመሳሳይ የተሳሳተ ዜና የአባታቸው ለሞት በሚያሰጋ ህመም ላይ መውደቅ ተዘግቦ የነበረ መሆኑን ለጦማሪው አውስተዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::