የመረጃ አንጣሪ ባለሙያዎች ላይ የሚደርሱ ዘርፈ ብዙ ጫናዎች!
የመረጃ አንጣሪ ባለሙያዎች (fact-checkers) በማህበራዊ ትስስር ገጾች እና በመደበኛ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የተዛቡና ሀሰተኛ መረጃዎች መከታተልና ማጣራት የየዕለት ክንውናቸው ነው። ፖለቲከኞች፣ ተጽዕኖ ተፈጣሪ ግለሰቦች እና ቡድኖች የሚናገሯቸው እና የሚጽፏቸው መረጃዎች ሀቅ ስለመሆናቸው ያመሳክራሉ እንዲሁም ፎቶግራፎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች አለመጨቆናቸውን (manipulate) ያጣራሉ።
የመረጃ አንጣሪ ባለሙያ ግቡ ዜጎች እወነተኛ መረጃ እንዲያገኙ በመረዳት በእውቀት ላይ የተመሰረቱ ውሳኔዎችን እዲያሳልፉ ማስቻል ነው። ይህም ግጭቶችን በመቀነስ የተረጋጋና መተማመን የሰፈነበት ምህዳር ለመጠር በእጅጉ ይጠቅማል።
አሁን አሁን እውነትን ለዜጎች ለማድረስ ጥረት የሚያደርጉ የመረጃ አንጣሪዎች የተዛባና ሀሰተኛ ዘገባን በሚያሰራጩ ግለሰቦች እና ቡድኖች የጥቃት ኢላማ እየሆኑ ስለመምጣቸው ከተለያዩ አገሮች የሚወጡ ሪፖርቶች ያሳያሉ። ማሸማቀቅ፣ ማስፈራራት፣ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ዘመቻዎችን መክፈት እና ሌሎችም የተዛቡና ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ ግለሰቦችና ቡድኖች መረጃ አንጣሪዎች እውነትን ለዜጎች ለማድረስ የሚደርጉትን ጥረት ለማደናቀፍ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
ይህ መሰሉ ጥቃት በተለይም በፕሬስ ነጻነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ በሚገኙ አገሮች ጎላ ብሎ ይታያል። በብራዚል መረጃ በማንጠር ስራ ላይ የተሰማራው ሉፓ በተቋሙ ባለሙያዎች ላይ ያነጣጠሩ በሺዎች የሚቆጠሩ አሸማቃቂ፣ አስፈራሪ ብሎም የግድያ ዛቻ የቀላቀሉ ትዊቶች እንደሚደርሱት ያስታወቀ ሲሆን በፊሊፒንስ የቬራ ፊልስ መረጃ አንጣሪ ተቋም ከባለሙያዎቹ አንጻር በየቀኑ ማስፈራሪያዎችን፣ ዛቻዎችን እና የስም ማጥፋት ዘመቻዎች እንደሚከፈቱባቸው ገልጿል።
በባንግላዴሽ ያቻይ የመረጃ ማንጠር ቡድን ባለሙያዎች ለደህንነታቸው በመስጋት ማንነታቸውን ደብቀው የሚሰሩ ሲሆን በኢራን የሮሃኒ ሜትር እና ፋክት ናሜህ መረጃ አንጣሪዎች ከአገራቸው ርቀው ሙያቸውን ይከውናሉ።
መረጃ አንጣሪዎችን ኢላማ ማድረግ በፕሬስ ነጻነት ደረጃቸው ከፍ ባሉ አገሮችም የሚታይ ሲሆን በጣሊያን፣ በፈረንሳይ እና በስፔን በግል እና በተቋም ደረጃ መረጃን በማንጠር ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች የዛቻ፣ የማስፈራራት እና የዘመቻዎች ሰላባ ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ተደምጠዋል።
እንዲህ አይነቱ እውነትን በማውጣት ስራ ላይ በተሰማሩ ባለሙያዎች ላይ የሚደረግ ጥቃት ዜጎች ትክክለኛ መረጃ እንዳያገኙ በማድረግ የተረጋጋና ሰላም የሰፈነበት ምህዳር ለመፍጠር እክል ይፈጥራል።
በመረጃ አንጣሪዎች አንጻር በሚደርሱ ጥቃቶች ተባባሪ ባለመሆን የተዛቡና የሀሰተኛ መረጃዎችን ስርጭት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ያግዙ።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::