የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶችን በተመለከተ እየተሰራጩ ያሉ የተሳሳቱ እና የተዛቡ መልእክቶች ጉዳይ!

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ የፈረንጆቹ 2020 ዓ.ም በመላው ዓለም ለሚገኙ የሰው ልጆች መልካም  አልነበረም። በወረርሽኙ ምክንያት በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ለቀናት እና ለሳምንታት በሆስፒታል አልጋዎች ለመተኛት ተገደዋል፤ የቤተሰብ አባሎቻቸውን እና በቅርብ የሚያውቋቸውን ሰዎች በሞት ተነጥቀዋል፤ ከስራ ተቀንሰዋል እንዲሁም ከማህብራዊ ኑሯቸው እና ከየዕለት እንቅስቃሴያቸው ተገድበዋል።

የወረርሽኙ መስፋፋት እና የሚያደርሰው ጉዳት አሁንም የቀጠለ ሲሆን በፈረንጆቹ 2021 ዓ.ም ዋዜማ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶች የመገኘታቸው ዜና መሰማቱ ለበርካቶች እፎይታን እና ተስፋን የጫረ ክስተት ሆኗል። ባለፉት ወራትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ በተለይም የአደጉ አገራት ዜጎች የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባትን ተከትበዋል።

ኢትዮጵያም በያዝነው አዲሱ የፈረንጆች አመት ማብቂያ 20ፐርሰንት የሚሆነውን ህዝቧን ለመከተብ ማቀዷን በጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ ሙሉቀን ዮሀንስ በቅርቡ የተናገሩ ሲሆን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ሁለት ወራት ለክትባት የምታውላቸው 9 ሚልዮን የኮሮና ቫይረስ የክትባት ብልቃጦችን ከአንድ ወር በሁዋላ ትረከባለች ብለዋል።

ይህ መልካም ዜና ቢሆንም የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶችን በተመለከተ የተሳሳቱ፣ የተዛቡ እና በሴራ ትንታኔ የተለወሱ ትርክቶች (conspiracy theories) በማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት በመሰራጨት ላይ መሆናቸውን ኢትዮጵያ ቼክ ተመልክቷል።

የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባትን በተመለከተ በመሰራጨት ላይ ከሚገኙ የተሳሳቱ፣ የተዛቡ እና በሴራ ትንታኔ ከተለወሱ ትርክቶች መካከል የክትባቱን ውጤታማነት ሰዎች እንዲጠራጠሩ የሚገፋፉ በሳይንስ ያልተደገፉ መልዕክቶች እንዲሁም ክትባቱን “666”፣ “ኢሊሙናቲ” ወዘተ ከሚሉ በሴራ ተንታኞች ከተለመዱ ቁጥሮችና ቃላት ጋር የሚያገናኙ ትርክቶች ይገኙባቸዋል።

እንዲህ ያሉ የተሳሳቱ፣ የተዛቡ እና በሴራ ትንታኔ የተለወሱ መልዕክቶች ዜጎች በክትባቶች ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው እና ላለመከተብ እንዲወሱ በማድረግ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ያደናቅፋሉ፣ በዜጎች ጤና ላይም ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል።

ስለሆነም የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶችን በተመለከተ የዓለም የጤና ድርጅት፣ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር፣ የህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲቲዩት እና የጤና ባለሙያዎች የሚሰጧቸው መረጃዎችን በመከታተል ከሀሰተኛ፣ ከተዛቡ እና በሴራ ትንታኔ ከተለወሱ ትርክቶች ራስዎን ያርቁ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::